በአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ ሌቦች 30 ሚሊዮን ዶላር ሰረቁ

ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ፣ ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚገኝ የጥሬ ገንዘብ ማከማቻ 30 ሚሊዮን ዶላር ተሰረቀ።

ድርጊቱ የተፈፀመው ባለፈው እሑድ በተከበረው የፈረንጆቹ የፋሲካ በዓል ዕለት ሲሆን ወንጀሉ መፈፀሙ የታወቀው በማግስቱ ነበር።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የ30 ሚሊዮን ዶላር ስርቆቱ በሎስ አንጀለስ ታሪክ ከተፈፀሙ ከፍተኛው ዝርፊያዎች አንዱ ነው።

የሎስ አንጀለስ ፖሊስ መሥሪያ ቤት እና የአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ (ኤፍቢአይ) ጉዳዩን በጥምረት እየመረመሩ ነው።

ሌቦቹ በሳን ፈርናንዶ ቫሊ በሚገኘውና የአካባቢው የንግድ ተቋማት ገንዘብ በጥሬው ወደሚያስቀምጡበት የገንዘብ ማከማቻው ዘልቀው ሲገቡ ምንም የጮኸ የማንቂያ አላርም አልተሰማም፤ መግባታቸውንም የሚያውቅም አልነበረም።

ይህ ዘራፊ ቡድን በሕንጻው ጣሪያ በኩል እንደገቡ እንደሚታመን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች የገንዘብ ማከማቻውን ሲከፍቱት ገንዘቡ አለመኖሩን ያዩት ድርጊቱ በተፈፀመ ማግስት ሰኞ ዕለት ነበር። ካዝናው መሰበሩን የሚያሳይም ምንም ምልክት አልነበረም።

እንደ አገሪቷ ሚዲያ ከሆነ ስርቆቱ የተፈፀመው ሲይልማር አካባቢ በሚገኘው ጋርዳ ወርልድ በተባለ ተቋም ላይ ነው።

ከላይ በሔሊኮፕተር የተነሳ ምስልም በሕንጻው ጎን ላይ ቀዳዳ እንዳለ እና በአቅራቢያ ያለ ፍርስራሽ አሳይቷል። ሆኖም ይህ ከወንጀሉ ጋር ይገናኝ አይገናኝ ግልጽ አይደለም።

ይህ ዘርፊያ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከተፈፀመ ስርቆት ከፍተኛው መሆኑን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

እንደ ጋዜጣው ከሆነ በሎስ አንጀለስ ከተማ እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 1997 ደንባር አርሞርድ ከተባለው ተቋም የተዘረፈው ከፍተኛው ጥሬ ገንዘብ 18.9 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በዚህ ድርጊት የተሳተፉ የቀድሞ ሰራተኛን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ታስረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ 2022 ደግሞ እሑድ ዕለት ዝርፊያ ከተፈፀመበት አካባቢ በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ የጥይት መከላከያ ያለው የጦር ተሽከርካሪ ተዘርፎ ነበር።

በወቅቱ የነበሩ ጥበቃዎች በተዘናጉበት ጊዜም ዘራፊዎቹ ውድ የሆኑ ጌጣጌጦች እና የከበረ ድንጋይ የያዙ በርካታ ሻንጣዎችን ወስደዋል።

እነዚህ የተሰረቁ ማዕድናት 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሲሆን እስካሁን ድርጊቱን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋለ አካል የለም።

ባለፈው ዓመትም በቶሮንቶ አየር ማረፊያ ከ15 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚያወጣ ወርቅ ተሰርቋል።

የአውሮፕላን ዕቃ መጫኛ ኮንቴነር ዕቃዎቹን ይዞ አየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ወደ አውሮፕላን እቃ መጫኛው እየሄደ ባለበት ወቅት ድርጊቱ እንደተፈፀመ ፖሊስ ያምናል።

ይህም በካናዳ ታሪክ የተፈፀመ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝርፊያ ነው።