የቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ለበረራ እየተነሳ ሳለ የሞተሩ ሽፋን ተገንጥሎ ወደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ሳውዝዌስት አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ለበረራ እየተነሳ ሳለ የሞተሩ ሽፋን ከወደቀ በኋላ ምርመራ ተጀመረ።
ከቴክሳስ ሂዩስተን እየተነሳ የነበረው አውሮፕላን የሞተር ሽፋን ሲገነጠል የአውሮፕላኑን ክንፍ መትቷል።
135 መንገደኞችን እና 6 የአውሮፕላኑ ሠራተኞችን ይዞ የነበረው አውሮፕላን ተጨማሪ ችግር ሳይደርስበት ዴንቨር አየር ማረፊያ ማረፍ ችሏል።
በዚህ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ የተፈጠረው ክስተት ያጋጠመው ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ላይ የደኅንነት ጥያቄ እየተነሳበት ባለበት ወቅት ነው።
ሳውዝዌስት አየር መንገድ ተገንጥሎ የወደቀው የሞተር መሸፈኛ በአየር መንገዱ ባለሙያዎች የሚጠገን የአውሮፕላን አካል መሆኑን አረጋግጦ፤ ሞተር መሸፈኛው እንዴት ተገንጥሎ ሊወድቅ እንደቻለ ምርመራ ጀምሪያለሁ ብሏል።
አየር መንገዱ በክስተቱ ደንበኞች ላጋጠማቸው መጉላላት ይቅርታ ጠይቆ፣ የደንበኞች እና ሠራተኞችን ደኅንነት ማረጋገጥ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብሏል ባወጣው መግለጫ።
የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር እንዳለው የሞተር መሸፈኛው የተገነጠለበት አውሮፕላን የተመረተው እአአ 2015 ነው።
ይህ ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ብዙ የደኅንነት ጥያቄ እየተነሳበት ያለው የቦይንግ 373-800 ማክስ አውሮፕላን የቀደመ ስሪት ነው።
እነዚህ ሁለቱም አውሮፕላኖች በጄኔራል ኤሌክትሪክ ኤሮስፔስ እና በሳፍራን ኤየርክራፍት ኢንጀንስ ኩባንያዎች ጥምረት የሚመረተው ሲኤፍኤም56 ሞተር ነው የተገጠመላቸው።
ክስተቱን ተክትሎ ቢቢሲ ለቦይንግ ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ሳውዝዌስት አውሮፕላን ተሳፋሪዎቹን ከሦስት ሰዓታት መዘግየት በኋላ በሌላ አውሮፕላን ወደ መዳረሻቸው መላኩን አስታውቋል።
የአሜሪካው አውሮፕላን አመራች ኩባንያው ቦይንግ በ737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ በሚያጋጥሙ ክስተቶች እና አደጋዎች በደኅንነት ደረጃው ላይ ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች የሆኑ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ተከስክሰው 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
እነዚህን አደጋዎች ተከትሎ በመላው ዓለም ከ18 ወራት በላይ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው ቆይተው ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ የአላስካ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ተገንጥሎ መውደቁ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
አላስካ አየር መንገድ ይህን ክስተት ተከትሎ ለደረሰበት ኪሳራ ቦይንግ ለአየር መንገዱ 160 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ከፍሎታል።