'የአምባገነኗ' ዮዲት ጉዲት ታሪክን የሚዳስሰው የባና ደስታ የድምፅ ድራማ

ባና ደስታ

የፎቶው ባለመብት, Jay Graham

ታዋቂ የሆሊውድ ተዋናዮችን ያሳተፈ 'ዘ አቢሲኒያን' (አቢሲኒያውያን) የተሰኘ የድምጽ ድራማ ተለቋል።

ድራማው ጥንታዊ እና የዓለማችን የቁንጮ ማማ ላይ ከደረሱት አንዱ በሆነው የአክሱም ስልጣኔ ላይ የሚያጠነጥን ነው።

ጸሐፊ ተውኔቷ ባና ደስታ በቅርቡ ይህንን ጥንታዊ የአፍሪካ ስልጣኔን በድምጽ ድራማ (ኦዲዮ ድራማ) በማምጣት ሕይወት ዘርታበተለች።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አወዛጋቢ የምትባለውን አምባገኗን ንግሥት ዮዲት እንዲሁም የሁለቱ ልጆቿ ታሪክ ዋነኛ የድርሰቷ ማዕከል ናቸው።

"ድራማው ጥሩ እና አዝናኝ ነው፤ ታዳሚዎች እንዲዝናኑ ከመፈለግ እንዲሁም ስለ አፍሪካ ያላቸውን ግንዛቤ ሌላ ዕይታ ለመስጠት ነው" ትላለች ባና።

"አህጉሪቱ ቅኝ ግዛት ባልተገዛችበት ወቅት የበለጸጉ ማህበረሰቦች የነበሩበትን ወቅት የሚዘክር ጽሑፍ ለመጻፍ ፈልጌ ነበር" ስትል ታስረዳለች።

በድምጽ ብቻ የተሰራው ይህ ድራማ 'ዘ አቢሲኒያን' (አቢሲኒያውያን) ይሰኛል።

መቼቱንም ያደረገው በአምስተኛው ክፍለ ዘመን በነበረው የአክሱማይት ግዛት (የአክሱም ኪንግደም) ላይ ነው።

የአክሱም ግዛት በከፍታው ዘመን በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አካባቢን ይዞ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡባዊ ሳዑዲያ አረቢያ፣ ምዕራብ የመን ድረስ የሚዘረጋ እና ከፍተኛ ተጽእኖ የነበረው ስልጣኔ ነው።

የአክሱም ስልጣኔ ለአንድ ሺህ ዓመት እንደቆየ የሚታመን ሲሆን ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት 100 ዓመተ ዓለም እስከ 960 ድረስ ዓመተ ምህረት ቆይቷል።

ክርስትና መጀመሪያ ወደ አፍሪካ የገባበት እና የአህጉሪቱ የመጀመሪያ ሳንቲሞች የታተመበት ስፍራ ነው። አክሱም በህንድ እና በሜድትራንያን መካከል ባለው የንግድ መስመር ማዕከል ትገኝ የነበረ ሲሆን፤ መርከቦቿ የቀይ ባህርን በአዱሊስ ወደብ እና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ በኩል ያሉ መስመሮችን ይቆጣጠሩ ነበር።

አክሱም በሶስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት ከፋርስ፣ ሮም እና ቻይና ጋር የዓለማችን አራቱ ታላላቅ ግዛቶች እንደ አንዷ ትቆጠር ነበር።

"አክሱም ከነዚህ ስልጣኔዎች ሙሉ በሙሉ የተገለለች ያህል ነው የሚሰማኝ። ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መገኛ ናት። ነገር ግን በዓለም አቀፉ ታሪክ ውሰጥ እንዳልተካተተ ይሰማኛል" ትላለች ባና።

የድራማው ጸሐፊ ባና ደስታ
የምስሉ መግለጫ, የድራማው ጸሐፊ ባና ደስታ
የንግስት ዮዲትን ገጸ ባህርይ ወክላ በድምጽ የምትጫወተው የባፍታ ሽልማት እጩዋ እና ታዋቂዋ የፊልም ተዋናይት ዳኒየል ዴድዋይለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የንግስት ዮዲትን ገጸ ባህርይ ወክላ በድምጽ የምትጫወተው የባፍታ ሽልማት እጩዋ እና ታዋቂዋ የፊልም ተዋናይት ዳኒየል ዴድዋይለር

አሜሪካ ውስጥ የተወለደችው ባና እናቷ ከትግራይ ኢትዮጵያ ሲሆኑ አባቷ ደግሞ ኤርትራዊ ናቸው። የቤተሰቦቿ የትውልድ ስፍራ የቀድሞዋ አክሱም ግዛት እምብርት ከሆኑ አካባቢዎች መሆናቸው ለሷ ትልቅ ስፍራ አለው።

"በእውነቱ መነሻ የሆነኝ ቅድመ ቅኝ ግዛት የነበረውን ዘመን የበለጠ ለማወቅ ስለፈለግኩ ነው። ለዚህ ደግሞ በጣም ጥሩ ቦታ የዘር ሀረጌ እንዲሁም የራሴ ቅርስ ነው ብዬ አሰብኩ" ስትል ትገልጻለች።

በሸሪፋ አል ዳይሬክት የተደረገው አቢሲኒያውያን የድምጽ ድራማ የተለቀቀ ሲሆን የባና የመጀመሪያ ሥራ ነው። ጽሑፉ ታሪካዊ እውነታን ከጸሐፊዋ ምናብ ከመነጩ ሁነቶች ጋር በማዋሃድ አስቂኝ እና አሳዛኝ ክስተቶችን አጣምሮ ይተርካል።

ድርሰቱ "ሰዎች በከፍተኛ ለውጥ ወቅት ሰብዓዊነታቸውን አጥብቀው ስለሚይዙባቸው መንገዶች ጭምር ነው" ትላለች ባና።

ታሪኪ በመንታ መንገድ ላይ የነበረውን የንግሥት ዮዲትን ንጉሣዊ አገዛዝ ይቃኛል።

ንግሥት ዮዲት ከመንታ ልጆቿ ካሌብ ወይም ንጉስ ዙፋኗን የሚወርሰው የትኛው እንደሆነ መወሰን ያለባትን ጉዳይ ማዕከል አድርጓል። በአገዛዟ የነበሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች፣ እንዲሁም ከሃይማኖት እና መብት ጋር የሚጋጩ እምነቶችን ይዟል። የፍቅር ታሪኮችን እንዲሁም አካቷል።

የንግሥት ዮዲትን ገጸ ባህርይ ወክላ በድምጽ የምትጫወተው የባፍታ ሽልማት እጩዋ እና ታዋቂዋ የፊልም ተዋናይት ዳኒየል ዴድዋይለር ናት።

የአክሱም ሐውልት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአክሱም ሐውልት

የዮዲት ገጸ ባህርይ መሰረት ያደረገው በኢትዮጵያ ታሪክ በአውዳሚነት፣ በጭካኔና በአምባገነን የሚጠቅሳት ንግሥት ዮዲትን ነው። ዮዲት ከስሟ፣ ከትውልዷ እንዲሁም የንግሥናዋን ዘመን ጨምሮ በርካታ የሚጣረሱ ታሪኮች ባለቤት ናት። ውድም የተባለውን የአክሱም ንጉሥ ለመውጋት ጦሯን ያሰማራች፣ ለአክሱም ስልጣኔ መውደቅ ምክንያት የሆነች፣ አምባገነን እና ጨካኝ አድርገው ታሪክ ጸሐፊዎች ይስሏታል። ባና ለጽሑፏ ምርምር ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ባቀናችበት ወቅት የሰማችው ይህንኑ ነው።

ለገጸ ባሕርይዋም ጥሩ መነሻ እንዳገኘች ተሰማት።

በዚህ የታሪክ ዘመን ሴት አምባገነን መሪ መሆኗም የበለጠ የወደደችው ሃሳብ ሆነ።

ታዋቂው አፍሪካዊ-አሜሪካዊ ጸሐፊ በአንድ ወቅት አርቲስቶች "ስሜታዊ ወይም መንፈሳዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ናቸው" ሲል የተናገረ ሲሆን ባናም ድርሰቱን ስትጽፍ ይህንኑ ባስተጋባ መልኩ ነበር።

"የሰውን ስሜቶች ሙሉ ገጽታ፣ የእነዚህን ገጸ ባህርያት የግል ስሜቶች፣ ከአደባባይ ሕይወታቸው ጀርባ እንደ ሰው የሚታገሏቸውን ነገሮች ለመዳሰስ እፈልግ ነበር" ብላለች።

ንግሥት ዮዲት በሕይወቷ ብዙ ፍቅር እንደሌላት ባና ይሰማታል።

"ለዓለም የምትሰጠው ምላሽ እንደ ህይወት አጋር ክብር እንዳልተሰጣት ነው። ለመሪነት እንደተመረጠ ወይም በዓለም ላይ ቦታ እንዳላት አይሰማትም" ስትል ባና ትናገራለች።

በሴቶች ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመቅረፍ የተጻፈው እና በዚሁ ድራማ የተካተተው ሌላኛዋ ሴት ገጸ ባህርይ ማክዳ ናት። በብሪጅተን ፊልም ዝናን የተጎናጸፈችው ኢትዮጵያዊ- ናይጄሪያዊቷ ታዋቂዋ ተዋናይት አርሴማ ቶማስ የሷን ገጸ ባህርይ ወክላ ትጫወታለች።

የኢትዮጵያ ጥንታዊ መጽሃፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ገጸ ባህርይዋ መሰረት ያደረገው የአባቷን ዕዳ ለመክፈል በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ በአገልጋይነት ስለተቀጠረች ሴት ነው።

ማክዳ "አስተሳሰቧ የመጠቀ፣ ከነበረችበት ስፍራ ዘልቃ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ የነበራት" ናት።

እነዚህ ታሪኮች በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታቸውን ቢያደርጉም በጽሑፎቹ ዘመናዊነት እና ሁሉንም መንካት እንዲችሉ ተደርገው ነው የተቃኙት።

በተለይም የንግሥት ዮዲት ገጸ ባህርይ በቁም ነገር መሃል በአሽሙር አስተያየት ጣል ማድረግ ትወዳለች።

ለዚህ የድምጽ ድራማ የኢትዮ- ጃዝ ሙዚቃ ማጀቢያውን የሰሩት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው ሙዚቀኛ ዲኤ መኮንን፣ አንድሪው ኦርኪን እንዲሁም ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ክብሮም ብርሃኔ ተሳትፎበታል።

ሙዚቃው ለተውኔቱ ገራሚ የሆነ ማጀቢያ እንደሰጠው ባና ትናገራለች።

"በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች የጥንቱን የሚያስታውስ ነገር አላቸው፤ ከዚያም ጃዝ ሲጨመርበት የኋላውን እና የአሁኑን የሚያሰላስል መልክ ይሰጠዋል" ብላለች።

የቶኒ ሽልማት አሸናፊው አንድሬ ደ ሺልፈድስ

የፎቶው ባለመብት, Lia Chang

የምስሉ መግለጫ, የቶኒ ሽልማት አሸናፊው አንድሬ ደ ሺልፈድስ

የቶኒ ሽልማት አሸናፊው አንድሬ ደ ሺልፈድስ በአቢሲኒያውያን ውስጥ የነበረውን ተሳትፎ ሲገልጸው "ወደ ጥንት ባህል የመመለስ ዕድልን ያሳየኝ" እንዲሁም "ጥበብ ሕይወትን የመለወጥ ታላቅ ኃይል" ያለው ምሳሌ ነው ይላል። የጥቁር ዳያስፖራ ተዋናዮች እነዚህን ገጸ ባህርያት መጫወታቸው ለባና ወሳኝ ጉዳይ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2021 የአፍሪካ መሪ የፊልም ፌስቲቫል በሆነው ፌስፓኮ ምርጥ የተዋናይት ዘርፍ ሽልማትን የተጎናጸፈችው ዘይነብ ጃህም በዚህ ድራማ ተሳታፊ ናት።

በተጨማሪም የትወና ሕይወቱን በዩናይትድ ኪንግደም ሮያል ሼክስፒር ኩባንያ ጋር የጀመረው ቹክውዲ ኢውጂ፣ በብሮድዌይ ተውኔቶቹ እና ኮንታጂዮን በሚለው ፊልም የሚታወቀው ጄምስ ብራኖን የዚህ ድራማ ተዋናዮች ናቸው።

"ሁሉም ተዋናዮች ያላቸው ተሰጥኦ አስደናቂ ነው" የምትለው ባና "ይህ ለብዙ ጀማሪ ደራሲዎች እንደማይሆን አውቃለሁ። ለዚህ ነው ምስጋናዬ ላቅ ያለው" የባና ቀጣይ አላማ አቢሲኒያውያንን ወደ ቲያትር መድረክ ማምጣት ይሆናል።