በፈቃዳቸው ከአሜሪካ ለሚወጡ ሕገወጥ ስደተኞች ገንዘብ ሊሰጥ ነው

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሕገወጥ ስደተኞችን ለመያዝ እና ከአሜሪካ ለማባረር እየተተገበረ ባለው ዕቅድ ውስጥ በፈቃዳቸው ለሚመለሱ ገንዘብ ሊሰጥ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት የሚያባብራቸው ሕገወጥ ስደተኞች አሜሪካንን ለቀው ለመውጣት ከተስማሙ አንድ ሺህ ዶላር እና የመጓጓዣ ወጪያቸውን እንደሚሸፍን አስታውቋል።

የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ባለሥልጣን ክሪስቲ ኖም ይህንን የመንግሥታቸውን ሃሳብ ይፋ ሲያደርጉ እንደተናገሩት "ከመታሰር ለመደዳን በእራስ ፈቃድ ከአሜሪካ ለመውጣት መወሰን፣ አስተማማኝ እና ወጪን የሚቆጥብ መንገድ ነው" ብለዋል።

ይህንን ሃሳብ ተቀብለው ከአሜሪካ የሚወጡ ሰዎች አንድ ቀን በሕጋዊ መንገድ ሊመለሱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚችል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ወዲህ አወዛጋቢውን በጦርነት ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለውን ሕግ ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕገወጥ ስደተኞችን ማሰር እና ከአገራቸው ማስወጣት ጀምረዋል። ነገር ግን አንዳንዶቹ እርምጃዎቻቸው ሕጋዊ ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።

አሁን በቀረበው በራስ ፈቃድ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ከአሜሪካ ለመውጣት የሚመዘገቡ ሰዎች በኢሚግሬሽን ሕግ አስከባሪዎች ተይዘው ከሚታሰሩት መካከል እንዳይካተቱ እንደሚደረግ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ባሠራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

ባለሥልጣኑ እንዳለው የመጀመሪያዎቹ "ሕገወጥ ስደተኞች" የቀረበላቸውን ሐሳብ ተቀብለው ከቺካጎ ወደ ሆንዱራስ የሚያደርስ የአውሮፕላን ቲኬት ተስጥቷቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ይህ ሃሳብ ተግባራዊ የሚሆነው ፈቃደኛ ግለሰቦች ወደ መጡባቸው አገራት መመለሳቸውን ለማረጋገጥ በተዘጋጀው መተግበሪያ ለሚጠቀሙ ስደተኞች ላይ መሆኑን ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ይህን አሠራር "ክብርን የሚያስጠብቅ" መስመር በማለት፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱንም ወጪን ይቀንሳል ተብሏል።

አንድን ስደተኛ ለመያዝ፣ በእስር ለማቆየት እና ከአገር ለማባረር በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው ወጪ ወደ ከ17 ሺህ ዶላር በላይ መሆኑ ተንግሯል።

በዚህ ሂደት ከአሜሪካ የሚወጣ ስደተኛ አንድ ቀን ሕጋዊ ሆኖ ወደ አገሪቱ እንዲመለስ ሊደረግ መቻሉ እራሱ አንዱ የአሜሪካንን ጥቅም ማስጠበቂያ መንገድ መሆኑን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል።

"ከሚመለሱት ጋር አብረን እንሠራለን፤ ስለዚህም ምናልባት አንድ ቀን ብዙ መልፋት ሳያስፈልጋቸው በአገራችን እንዲኖሩ የምንፈልጋቸው ዓይነት መልካም ሰዎች ከሆኑ ተመልሰው ሊመጡ ይችላሉ" ሲሉ ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ይህ ዕቅድ ግን ትችት ገጥሞታል። የዲሞክራቶች የምክር ቤት አባል የሆኑት አድሪያኖ ኤስፔይላት በኤክስ ገጻቸው ላይ "ሰዎችን ከአገር እንዲወጡ ጉቦ መስጠት የለብንም። ሁሉም እንደቤቱ የሚያየው አገር መገንባት አለብን" ሲሉ ጽፈዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና አጋሮቻቸው ወደ አሜሪካ በድንበር በኩል የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መቀነሱን በመጥቀስ በሦስት ወር ውስጥ የወሰዱትን እርምጃ እያደነቁ ነው።

በመጋቢት ወር በሜክሲኮ በኩል ወደ አሜሪካ ሲያቋርጡ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሰባት ሺህ ብዙም ያለፈ አለመሆኑን በመጥቀስ በከፍተኛ ሁኔታ አሃዙ ዝቅ ማለቱን የአገሪቱ የድንበር ቁጥጥር መሥሪያ ቤት ያወጣው መረጃ አሳይቷል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው በአሜሪካ ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ይዞ በማሰር እርምጃ ምክንያት የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ዕቅዳቸው እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ግን የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር እስካሁን ቃል በገባው መሠረት በርካታ ስደተኞችን ከአገር አላስወጣም። በተጨማሪም ትራምፕ በአሜሪካ በመወለድ የሚገኘውን ዜግነት ለማስቀረት ያደረጉት ሙከራ በፍርድ ቤት ታግዷል።