የአሜሪካን ምሥጢር ለሶቪየት አሳልፎ ከባድ ጉዳት ያደረሰባት የሲአይኤ ሰላይ

አልድሪች አሜስ ለአሥርታት ለሶቭየት ኅብረት ምሥጢራዊ መረጃ ሲሸጥ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አልድሪች አሜስ ለአሥርታት ለሶቭየት ኅብረት ምሥጢራዊ መረጃ ሲሸጥ ነበር።

አልድሪች አሜስ ለአሥርታት ለሶቭየት ኅብረት ምሥጢራዊ መረጃ ሲሸጥ ነበር። ከ100 በላይ ምሥጢራዊ የስለላ ሥራዎች አከናውኗል።

10 የሚደርሱ ምዕራባውያን የስለላ ባለሙያዎች በአልድሪች ምክንያት ተገድለዋል።

ለሁለት ወገን የሚሰልለው አልድሪች እአአ በ1994 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ኦልግ ጎርዲቭስኪም ለሁለት ወገን ነው የሚሰልለው። በለንደን የሩሲያ ስለላ ተቋም ኬጂቢ ኃላፊ ሳለ በምሥጢር ለዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ተቋም ኤም16 በጎን ይሠራ ነበር።

አንድ ቀን ራሱን ሞስኮ አገኘው። ለአምስት ሰዓታት ጥያቄ ተደርጎለት፣ ተደብድቦ ደክሞ ነበር።

ሊገደል ትንሽ ሲቀረው ኤም16 በመኪና ደብቆ ከሞስኮ አስወጣው።

"ለዘጠኝ ዓመት ያህል ማን እንዳጋለጠኝ ለማወቅ ስሞክር ነበር። አሁን ግን ደረስኩበት" ይላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ባልደረባ የነበረው አልድሪች በአሜሪካ ፍርድ ቤት ሲቀርብ እውነታው ወጣ።

"የሲአይኤ ሰላይ የሆኑ የሶቪየት ልዑካን ያውቁኛል" ሲል አልድሪች በፍርድ ቤት ቃሉን ሰጠ።

ሰላሳ 30 ለምዕራባውያን አገራት የሚሠሩ ሰላዮችን ማንነት እንዳጋለጠ እና ወደ 100 ኦፕሬሽኖችን እንዳከሸፈ አምኗል።

ኬጂቢ የሚውያውቀው ኮሎኮል (ደወል) በሚል ቅጽል ስም ነው። ክህደት የፈጸመባቸው 10 የሲአይኤ የስለላ ባልደረቦች ተገድለዋል።

ይህም ለ20 ዓመታት ለምዕራባውያን መረጃ ያቀብል የነበረውን የሶቭየት የወታደር ኃላፊ ዲሚትሪ ፖሊኮቭን ይጨምራል።

በአሜሪካ ታሪክ አደገኛው የሚባለው የኬጂቢ ሰላይ አልድሪች ያለ አመክሮ የዕድሜ ልክ እስራት ሲፈረድበት ይግባኝ መጠየቅ እንደማይችል ተገልጿል።

በሲአይኤ የሶቭየት የአጸፋ ስለላ መሪ ሳለ ብዙ ጉዳት በአሜሪካ አድርሷል። አሜሪካ በሩሲያ ያላትን የስለላ ኦፕሬሽኖች ያውቅ ነበር።

ከሌሎች ምዕራባውያን ሰላዮች ጋር መረጃ ይለዋወጥ ነበር።

ኦልግ እንደሚለው አሜሪካውያን ዝርዝር መረጃ ስለሚሰጡ እሱም በምላሹ መረጃ ያቀብል ነበር። ከአልድሪች ጋር የተዋወቁትም በዚህ ሥራ ወቅት ነው።

አልድሪች የሚቀበለውን መረጃ ለኬጂቢ እያስተላለፈ እንደነበር አላወቀም።

የአልድሪች አባት ለሲአይኤ ይሠሩ ስለነበር ሥራውን ያገኘው ወጣት ሳለ ነበር። ሲአይኤን ለመክዳት የወሰነው ለአቋሙ ሲል ሳይሆን ለገንዘብ መሆኑ ኋላ ላይ ተደርሶበታል።

ሲአይኤ ትሠራ ከነበረች ባለቤቱ ናንሲ ሰግባርት ጋር ቱርክ ነበር መጀመሪያ ላይ የተመደቡት። የስለላ ባለሙያዎች የመመልመል ኃላፊነት ነበር የተሰጠው።

እአአ በ1972 ወደ ሲአይኤ ተመለሰ። ሩሲያኛ ተማረ። የሶቭየት ሰላዮችን እንዲሰልል ነበር የተፈለገው።

አባቱ ጠጪ ስለነበሩ ሥራቸውን መቀጠል አልቻሉም። አልድሪችም ከመጠን በላይ ይጠጣ ነበር።

እአአ በ1972 ሰክሮ አንድ የሲአይኤ ሰላይ ደርሳበታለች። ባቡር ላይ ምሥጢራዊ መረጃ ጥሎ ወርዶም ያውቃል።

እአአ በ1981 ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ተዘዋወረ። ጠጥቶ ሲያሽከረክር በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ለሲአይኤ ጥቆማ ተደርጎበታል።

ሲአይኤ ከመለመላት የኮሎምቢያ የባህል ልዑክ ከማሪያ ደል ሮሳርዩ ካሳስ ዴፕዩቲ ጋር የፍቅር ግንኙነት ከጀመረ በኋል ከባለቤቱ ጋር ለመፋታት ወሰነ።

እአአ በ1983 ወደ አሜሪካ ሲመለስ የሶቭየት የስለላ ክፍል ውስጥ ከፍተኛ የአመራር ቦታ ተሰጥቶት የሲአይኤ ኦፕሬሽኖች መረጃ ይደርሱት ነበር።

ከባለቤቱ ጋር ከተለያየ በኋላ ገንዘብ ይልክ ስለነበር እና አዲሷ ባለቤቱ ከፍተኛ ወጭ ታወጣ ስለነበር የገንዘብ ችግር ውስጥ ገባ።

ፍርድ ቤት ቃሉን ሲሰጥ እንደተናገረው ዕዳ ውስጥ ተዘፍቆ ነበር።

"ገንዘብ እፈልግ ነበር። ከዚያ ውጪ ምክንያት አልነበረኝም" ሲል ለኤፍቢአይ ባልደረባ ሌዝሊ ጂ ዋይዘር ተናግሯል።

አልድሪች እአአ በ1994 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, አልድሪች እአአ በ1994 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

እአአ በ1985 በዋሽንግተን ዲሲ ወደሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ሄደ። ለሲአይኤ የሚሠሩ የሩሲያ ሰላዮችን ስም ዝርዝር ሰጣቸው።

በምላሹ 50,000 ዶላር እንዲከፈለው ጠየቀ። ከዚያም በኋላ የመረጃ እና የገንዘብ ልውውጡ ለዘጠኝ ዓመታት ቀጠለ።

የሲአይኤ መረጃ መጥለፊያ መሣሪያዎችን፣ የሶቭየት ሚሳዔልን ሊመቱ የሚችሉ የሕዋ መሣሪያዎችን አቀማመጥ እና ሌሎችም ምሥጢራዊ መረጃዎች አሳልፎ ሰጠ።

ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘት የሥራው አካል ስለሆነ ማንም ሰው መረጃ እያስተላለፈ እንደሆነ አልጠረጠረም።

ምሥጢራዊ መረጃዎችን በድብቅ ቦታዎች እያስቀመጠ ሰላዮች ይረከቡትም ነበር። መረጃው የሚቀመጥበትን ቦታ የሚጠቁመው በቾክ የፖስታ ሳጥን ላይ ምልክት በማድረግ ነበር።

የሶቪየት ሰላዮች መረጃውን ከተረከቡ በኋላ የቾክ ጽሑፉን ያጠፉታል።

አልድሪች መረጃ በማሾለኩ ምክንያት በሶቭየት ይሠሩ የነበሩ ሁሉም የሲአይኤ ሰላዮች የት እንደሆኑ ተደርሶበታል። አሜሪካ የስለላ ኦፕሬሽኖቿን እንድታቋርጥም ተገዳለች።

 በአሜሪካ ታሪክ ይህን ያህል ጉዳት ያደረሰ ሰላይ የለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ታሪክ የአልድሪችን ያህል ጉዳት ያደረሰ ሰላይ የለም።

የአልድሪችን የወንጀል ምርመራ የተከታተሉት የኤፍቢአይ ባልደረባ ሌዝሊ ጂ ዋይዘር እንደሚሉት፣ በአሜሪካ ታሪክ ይህን ያህል ጉዳት ያደረሰ ሰላይ የለም።

"በአሜሪካ ታሪክ የእሱን ያህል ጉዳት ያደረሰ ሰላይ መኖሩን እጠራጠራለሁ። የሰዎች ሕይወት በእሱ ምክንያት ተቀጥፏል" ሲሉ ይገልጹታል።

እአአ በ1986 በሶቭየት ያሉ የሲአይኤ ሰላዮች ድንገት መጥፋት ሲጀምሩ ጥርጣሬ ተፈጠረ። አልድሪች ግን መረጃ መሸጡን አላቆመም።

2.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ከሶቪየቶች ለሚሰጣቸው ምሥጢራዊ መረጃ ተከፍሎታል። ዓመታዊ የሲአይኤ ደመወዙ 70,000 ዶላር ይደርስ ነበር።

በ540,000 ዶላር አዲስ ቤት ገዝቶ በከፍተኛ ወጪ ቤቱን ማሳመር ቀጠለ። ጃጉዋር መኪናም ገዛ።

እአአ በ1994 በኤፍቢአይ ባልደረባ ሌዝሊ ጂ ዋይዘር የታሰረውም ከዚህ በኋላ ነበር። ጥርጣሬን የፈጠው ቅንጡ አኗኗሩ እንደሆነም ተገልጿል።

በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ባለቤቱ ላይ ጠንካራ ፍርድ እንዳይጣል ተደራድሮ ከፖሊስ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ሆኗል።

ባለቤቱ ለሶቭየት በምሥጢር መረጃ እንደሚያቀብል ታውቅ ነበር። አምስት ዓመት ብቻ ታስራ ተለቃለች።

በሲአይኤ ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ እያለ ለሁለት አገራት በመሰለል ግንባር ቀደም የሆነው አልድሪች አሜስ ነው።

በኢንዲያና፣ ቴሬ ሀውቴ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ አሁንም ድረስ ይገኛል።

ምሥጢራዊ መረጃ አሳልፎ በመስጠቱ የሰዎች ሕይወት ቢቀጠፍም እስከ ዛሬ ድረስ በሥራው እምብዛም ሲፀፀት አልታየም።

የኤፍቢአይ ባልደረባ ሌዝሊ ጂ ዋይዘር "ስለ ራሱ ትልቅ አመለካከት ነው ያለው። ሰላይ መሆኑ አይፀፅተውም። መያዙ ግን ይቆጨዋል" ይላሉ።