ታዳጊዎች ያለዕድሜያቸው የወር አበባ እንዲያዩ የአየር ብክለት እንዴት ምክንያት ይሆናል?

ከእናቷ ጋር እየተራመደች ያለች ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ከፍተኛ ለሆነ የተበከለ አየር ተጋላጭ የሆኑ ታዳጊዎች የመጀመሪያ የወር አበባቸውን ያለጊዜያቸው የማየት አጋጣሚ እንዳላቸው ጥናት ይፋ አድርጓል።

ከቀደመው ትውልድ ጋር ሲነጻጸር ያለዕድሜያቸው የወር አበባ የሚያዩ ታዳጊዎች መበራከት ተመራማሪዎችን አሳስቧል።

አንድ አዲስ ጥናት በአሜሪካ የሚኖሩ ታዳጊዎች የመጀመሪያ የወር አበባቸውን ከትክክለኛው ዕድሜያቸው ቀድመው እንደሚያዩ አመልክቷል። ለዚህም ለተበከለ አየር መጋለጣቸው እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል።

ገና ለጋ በሆኑ ታዳጊዎች ላይ የጉርምስና ምልክቶች መታየታቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ ተመራማሪዎችን እያነጋገረ ይገኛል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ታዳጊዎች ከመቶ ዓመት በፊት ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር በአራት ዓመት ቀድመው የወር አበባ ማየት እንደሚጀምሩ ይገመታል።

ግንቦት ወር ላይ የወጣ አንድ መረጃ እንደሚያሳየው ከአውሮፓውያኑ 1950 እስከ 1969 ባሉት ዓመታት የተወለዱ ልጆች የመጀመሪያ የወር አበባቸውን ማየት የጀመሩት በ12.6 ዓመታቸው ነው።

ይህ ዕድሜ በ2000 መጀመሪያዎቹ በተወለዱ ልጆች ላይ በአማካይ ወደ 11. 9 ዝቅ ብሏል።

በተቀረው የዓለም ክፍልም ተመሳሳይ ሁኔታ ተስተውሏል።

የደቡብ ኮሪያ ተመራማሪዎች ከ2008 እስከ 2020 (እአአ) ባሉት ዓመታት ውስጥ ከስምንት ዓመታቸው በፊት የወር አበባ ማየት እና ጡት ማጎጥጎጥን ጨምሮ የጉርምስና ምልክቶችን የሚያዩ ታዳጊዎች ቁጥር በአስራ ስድስት እጥፍ መጨመሩ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

በአሜሪካ አትላንታ በሚገኘው ኢሞሪ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤውድሪይ ጋስኪንስ፣ በዝቅተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ባሉ እና በቁጥር አነስተኛ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የጉርምስና ዕድሜ ዝቅ ማለት በጉልህ እንደሚታይ ይገልጻሉ።

ሆኖም እንደ ጋስኪንስ ያሉ ተመራማሪዎችን የሚያሳስባቸው ዋናው ጉዳይ የጉርምስና ዕድሜ ቀድሞ መጀመር በኋላ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ታዳጊዎች ያለዕድሜያቸው ለአካለ መጠን መድረሳቸው ቀድመው እንዲያርጡ በማድረግ የመውለጃ የዕድሜ ክልልን ከማጥበቡ ባሻገር ዕድሜያቸውንም ያሳጥራል።

ያለጊዜ ለጉርምስና ዕድሜ መድረስ ለኦቫሪ እና ለጡት ካንሰር በሽታ፣ ከልክ ላለፈ ውፍረት እና ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ እንዲሁም ለልብ እና ተያያዥ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ከመጨመር ጋርም ይያያዛል።

ተመራማሪዎች ይህ ለምን እንደሆነ ለመረዳት እየጣሩ ነው።

በካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ፕሮፌሰር የሆኑት ብሬንዳ እስከናዚ፣ የሰውነት ህዋሶች እንደ ኦስትሮጂን ላሉ የፆታ ሆርሞኖች ሥርጭት ለረጅም ጊዜ የሚጋለጡ ከሆነ፣ ሆርሞኖች የሕዋሳትን ዕድገት ስለሚያነቃቁ ዕጢ የመከሰት ዕድልን ሊጨምር እንደሚችል የሚያሳይ ጽንሰ ሃሳብ መኖሩን ያስረዳሉ።

“ለረዥም ጊዜ ሆርሞኖች እየመነጩ መቆየታቸው ለሥነ ተዋልዶ አካላት ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን ከፍ እንደሚያደርጉ የሚያሳዩ ጽንሰ ሃሳቦችም አሉ” ብለዋል ፕሮፌሰሯል።

ከዚህም ባሻገር ያለዕድሜ መጎርመስ ማኅበራዊ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት ቀድመው ወደ ጉርምስና የሚገቡ ታዳጊዎች ቀድመው የግብረ ሥጋ ግንኙነት የመጀመራቸው ዕድል ሰፊ ይሆናል።

ይህም በርካታ ታዳጊዎች ላልተፈለገ እርግዝና እንዲጋለጡ ከማድረጉ ባሻገር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች አሳሳቢ ናቸው ይላሉ ፕሮፌሰር እስከናዚ።

ለመሆኑ የሕጻናት ዕድገት በዚህ መልኩ የፈጠነው ለምንድን ነው?

መንገድ ዳር ላይ ቆመው የሚያወሩ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተመራማሪዎች እንደሚሉት ያለጊዜያቸው ጉርምስና ላይ የሚደርሱ ሴቶች በጉልምስና እድሜያቸው ብዙ ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ከልክ ካለፈ ውፍረት እስከ የአየር ብክለት

ጉርምስና በሰውነታችን ውስጥ ባሉ ሃይፖታላሚክ ፒቱታሪ አድሬናል (ኤችፒኤ) እና ሃይፖታላሚክ ፒቱታሪ ጎናዳል( ኤችፒጂ) የተባሉ ሁለት ዘንጎች በሚፈጥሩት ሁለት ሰፊ የኮሙኒኬሽን ሥርዓቶች ይወሰናል።

እነዚህ ዘንጎች ሃይፖታላመስ የተባለውናን ረሃባችንን፣ ሙቀታችንን እና የተለያዩ ሆርሞን አመንጪ ዕጢዎችን ከሚቆጣጠረው የአንጎላችን ክፍል ጋር የሚገናኙ ናቸው።

ዘንጎቹ በተለያዩ ምክንያቶች በሚነቃቁበት ጊዜ ወደ አእምሮ ትዕዛዝ በማስተለለፍ የፆታ ሆርሞኖች እንዲመነጩ ያደርጋሉ።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋስኪንስ እንደሚሉት ከ20 ዓመታት በፊት ተመራማሪዎች ያለጊዜ መጎርመስ በልጅነት ከሚከሰት ከልክ ያለፈ ውፍረት ጋር ያያይዙታል።

ምክንያታቸውም በስብ ሕዋሳት የሚመነጩ 'አዲፖኪንስ' የተባሉ ፕሮቲኖች ሆርሞን አመንጪ ዕጢዎችን የሚቆጣጠሩትን እና ኤችፒኤ እና ኤችፒጂ የተባሉትን የኮሚዩኒኬሽን ሥርዓቶች እንዲነቃቁ ስለሚያደርጉ ነው።

በሳይክል የሚጓዙ ሁለት ታዳጊ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ የሚኖሩ ታዳጊ ሴቶች ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር በአራት ዓመት ቀድመው የወር አበባ ማየት ይጀምራሉ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሠሩ በርካታ ጥናቶች ደግሞ ሕጻናት ያለዕድሜያቸው ቀድመው ለመጎርመሳቸው ሌላም ምክንያት እንዳለ ጠቁመዋል - የአየር ብክለትን።

ይህ ጥናት የተሠራው በደቡብ ኮሪያ ተመራማሪዎች ነው። እንደ አይኪው ኢንዴክስ ከሆነ የደቡብ ኮሪያዎቹ ሴዑል፣ ቡሳን፣ ኢንቺኦን በዓለም ከፍተኛ የአየር ብክለት ካለባቸው 100 ከተሞች መካከል ይገኙበታል።

በሴዑል በሚገኘው ኢውሃ የሴቶች ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ የታተመ አንድ ጥናትም የአየር ብክለት እና ያለጊዜ ጉርምስና ምን እንደሚያገናኛቸው ለይቷል።

ያለዕድሜ ጉርምስና መንስኤ ከሆኑ በካዮች መካከል ከተሽከርካሪ ወይም ከፋብሪካዎች ወደ አየር የሚለቀቁ እንደ ሰልፈር ዳይኦክሳይድ፣ ናይትሮጂን ዳይኦክሳይድ፣ ካርቦን ሞኖክሳይድ እና ኦዞን የመሳሳሉ መርዛማ ጋዞች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 በድንጋይ ከሰል ፋብሪካዎች መስፋፋት ምክንያት በአየር ጥራትዋ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ፖላንድ ውስጥ በ1257 ሴቶች መረጃ ላይ በመመሥረት በሳይንስ ምሁራን የተደረገ ጥናት ለናይትሮጂን ጋዝ በከፍተኛ ሁኔታ መጋለጥ ከ11 ዓመት በፊት የወር አበባ እንዲመጣ ምክንያት መሆኑን አረጋግጧል።

በዚህ ጥናት ከእንጨት ማገዶ፣ ከፋብሪካዎች፣ ከአቧራ፣ ከደን ቃጠሎ፣ ከጄኔሬተር እና ከመሳሰሉት የሚወጡ በዐይን የማይታዩ እና ወደ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችም (particulate matter) ካለ ዕድሜ ለሚከሰት ጉርምስና እንደ መንስኤ ተለይተዋል።

ሕንዳውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአየር ብክለት ዘርፈ ብዙ የጤና ችግሮችን ከማስከተሉ በተጨማሪ በተፈጥሮ ሂደት ላይም ለውጥን አምጥቷል

እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 2023 ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋስኪንስ እና ባልደረቦቻቸው በአሜሪካ ያሉ ታዳጊዎች ከፍተኛ ለተባለ ፒኤም 2.5 በካይ ጋዞች እንደሚጋለጡ ደርሰውበታል።

በመሆኑም በእናታቸው ማህፀን እያሉም ሆነ በልጅነታቸው ለእነዚህ በካይ ጋዞች የሚጋለጡ ሕጻናት ያለዕድሜያቸው የመጀመሪያ የወር አበባቸውን የማየት ዕድል አላቸው።

“ፒኤም 2.5 በካይ ቅንጣጢቶች በቀላሉ ወደ ደም ሥራችን መግባት ይችላሉ። በሳንባችን እንስባቸዋለን። ልክ እንደ ሌሎች ትላልቅ ቅንጣጢቶች ማጥለል አሊያም መለየት ስለማንችል ወደ ተለያዩ የአካላችን ክፍሎች ይደርሳሉ። ፒኤም 2.5 በካይ ቅንጣጢቶች በእንግዴ ልጅ፣ በማህፀን ኅብረ ሕዋስ (ቲሹ) እና በኦቫሪ ውስጥ ይጠራቀማሉ። ከዚያም ወደ ሌሎች የአካል ክፍሎች ይዛመታሉ” ይላሉ ጋስኪንስ።

ከቤት ውስጥ ከተወሰደ የአየር ናሙና የተገኙ በካይ ቅንጣጢቶችን በማዋሃድ የተሠሩ ጥናቶች በእነዚህ ጥቃቅን ቅንጣጢቶች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች በልጆች የሥነ ተዋልዶ ዕድገት ውስጥ አስተዋፅኦ ባላቸው ሆርሞኖች በተለይም አንድሮጂን እና ኦስትሮጂን ላይ መነቃቃትን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አሳይቷል።

የእነዚህ ሆርሞኖች መነቃቃትም ያለጊዜ ጉርምስና እንዲፈጠር ያደርጋል። ያለጊዜ ለመጎርመስ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉም ይጠቀሳል።

ተባባሪ ፕሮፌሰር ጋስኪንስ እንደሚሉት ፒኤም 2.5 እና ሌሎች በካዮችን በተመለከቱ የወጡ መረጃዎች በከባቢያችን የሚለቀቁ ጎጂ ኬሚካሎች ወደ ሰውነታችን በመግባት እንዴት ሆርሞኖችን እንደሚያነቃቁ ከሚያሳዩ ምሳሌዎች አንዱ ነው።

የግል ንጽህና መጠበቂያ ምርቶችም ታዳጊዎችን ያለዕድሜ ለሚከሰት ጉርምስና እንደሚያጋልጣቸው ጋስኪንስ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር እስክናዚ በበኩላቸው እየተለዋወጠ ያለው ዓለም እና ይህ መለዋወጥ በልጆች ዕድገት ላይ እያሳደረ ስላለው ተፅዕኖ የማናውቀው ብዙ ነው ይላሉ።

የፕላስቲክ ቁርጥራጮች እና ብናኞች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በዚህ ረገድ እያስከትሉት ያለው ተፅዕኖ ብዙ አልተጠናም ብለዋል ፕሮፌሰሯ።

“ጉዳዩ ገና አልተነካም ብዬ ነው የማስበው። የአየር ንብረት ለውጥ፣ ልጃገረዶች ቶሎ እንዲያድጉ የሚደረግ ማኅበራዊ ግፊት የወር አበባ ሥርዓትን እንዴት እንደሚያዛባ ብዙ አናውቅም። ሆኖም ይህ ክስተት እውነት ነው፤ የሚታይ ነው።

“ታዳጊዎች ያለጊዜያቸው የወር አበባ የሚያዩበት ምክንያት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ኬሚካሎች፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት እና ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦዊና ጉዳዮች ተደማምረው በሚያስከትሉት ተፅዕኖ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።