መድሃኒትን በሚቋቋሙ ኢንፌክሽኖች ሳብያ የአፍሪካ ሕጻናት ለአደጋ መጋለጣቸውን አንድ ጥናት አመለከተ

ባክቴርያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በ2022 በዓለም ላይ ከሦስት ሚሊየን በላይ ሕጻናት አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም አቅም ባላቸው ኢንፌክሽኖች ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል ተብሎ እንደሚገመት አንድ ጥናት አመለከተ።

በአፍሪካ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚገኙ ሕጻናት አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም አቅም ባላቸው ኢንፌክሽኖች ሳብያ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውም ተረጋግጧል።

ኢንፌክሽን የሚያስከትሉ ረቂቅ ተሕዋስያን ቀስ በቀስ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ሲላመዱ እና ፈዋሽነታቸው ሲቀንስ ፀረ-ባክቴርያን የሚቋቋሙ ወይንም ደግሞ ኤኤምአር (AMR) በመባል የሚታወቀው ሁኔታ ይከሰታል።

በዚህም የተነሳ እንደ ባክቴሪያ፣ቫይረሶች፣ፈንገሶች እና ጥገኛ ተውሳኮች ያሉ ረቂቅ ተሕዋስያን ለመግደል የታለሙ መድኃኒቶች ቢኖሩም በሕይወት ሊተርፉ አልፎ ተርፎም ሊባዙ ይችላሉ።

ይህ በዓለም ሕዝብ ላይ ከተጋረጡ ትላልቅ የሕዝብ ጤና ስጋቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ተለይቷል።

ይህ አዲስ ጥናት ኤኤምአር (AMR) በልጆች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ያሳያል።

የዓለም ጤና ድርጅት፣ የዓለም ባንክን እንዲሁም ሌሎች ምንጮችን በመጠቀም የተሰራው ይህ ጥናት እአአ በ2022 ከመድኃኒት ከተላመዱ ኢንፌክሽኖች ጋር በተገናኘ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት መሞታቸውን አሳይቷል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ይህ አዲስ ጥናት በሦስት ዓመታት ውስጥ በልጆች ላይ ከኤኤምአር ጋር የተዛመዱ ኢንፌክሽኖች ከአስር እጥፍ በላይ መጨመራቸውን ያሳያል።

ተመራማሪዎቹ ይህ ቁጥር በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተባብሶ ሊሆን አንደሚቸል ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል።

የአንቲባዮቲኮች አጠቃቀም መጨመር

አንቲባዮቲኮች በርካታ ዓይነት የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖችን ለማከም ወይም ለመከላከል ያገለግላሉ።

እነዚህ መድሃኒቶች ከቆዳ ኢንፌክሽን እስከ የሳንባ ምች ድረስ ለማከም ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ ኢንፌክሽኑን ከማከም ይልቅ ለመከላከል ይሰጣሉ።

ለምሳሌ አንድ ሰው ቀዶ ሕክምና ካደረገ ወይም ለካንሰር የኬሞቴራፒ ሕክምና እየተከታተለ ከሆነ አንቲባዮቲክ እንዲወስድ ይደረጋል።

አንቲባዮቲኮች እንደ ጉንፋን እና ኮቪድ ያሉ በቫይረስ በሚመጡ ኢንፌክሽኖች ላይ ምንም ተጽእኖ የላቸውም።

ነገር ግን አንዳንድ ባክቴሪያዎች ከመጠን በላይ ጥቅም ላይ በመዋላቸው እና ተገቢ ባልሆነ አጠቃቀም የተነሳ አንዳንድ መድሃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ አዳብረዋል።

በአውስትራሊያ የሙርዶክ የሕጻናት ምርምር ኢንስቲትዩት አባል የሆኑት ዶክተር ያንሆንግ ጄሲካ ሁ እና የክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ሄርብ ሃርዌል እንዳሉት ከሆነ በጣም ከባድ ለሆኑ ኢንፌክሽኖች ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የታሰቡ አንቲባዮቲኮች አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ እድገት ታይቷል።

እአአ በ2019 እና 2021 መካከል "ወሳኝ የሆኑ አንቲባዮቲኮች" ተብለው የተለዩ መድሃኒቶችን በደቡብ ምስራቅ እስያ በ160 በመቶ እና በአፍሪካ በ126 በመቶ ጥቅም ላይ ውለው ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለከባድ ሕመም፣ በርካታ መድሐኒቶች የሚቋቋሙ ኢንፌክሽኖች ለማከም እንደ መጨረሻ የመፍትሄ ሕክምናዎች የሚወሰዱ "ለመጠባበቅያ የተቀመጡ አንቲባዮቲኮችን" በመጠቀም ደግሞ በደቡብ ምሥራቅ እስያ በ45 በመቶ እና በአፍሪካ 125 በመቶ ጨምሯል።

እየቀነሱ የመጡ አማራጮች

ተመራማሪዎቹ ባክቴሪያዎች መድሃኒትን የመቋቋም አቅም ካዳበሩ፣ ብዙ መድሃኒት የሚቋቋሙ ኢንፌክሽኖችን ለማከም የሚኖረው አማራጭ እያነሰ ካልሆነም እየጠፋ እንደሚሄድ አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰር ሃርዌል ግኝታቸውን በዚህ ወር መጨረሻ በቪየና በሚገኘው የአውሮፓ ክሊኒካል ማይክሮባዮሎጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ኮንግረስ ላይ አቅርበዋል።

" ኤኤምአር (AMR) ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው። ሁሉንም ይጎዳል። ይህንን ጥናት የሰራነው ኤኤምአር ሕጻናትን የሚጎዳበት ያልተመጣጠነ መንገድ ላይ በማተኮር ነው" ሲል ከስብሰባው በፊት ተናግረዋል።

"በዓለም ዙሪያ ከፀረባክቴሪያ መከላከያ ጋር በተያያዙ ሦስት ሚሊዮን ሕጻናት እንደሚሞቱ እንገምታለን።"

ለኤኤምአር መፍትሄ አለ?

የዓለም ጤና ድርጅት ኤኤምአርን በጣም አሳሳቢ ከሆኑ የዓለም የጤና ስጋቶች አንዱ ሲል ይገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ሃርዌል በቪየናው ጉባዔ ላይ ሲናገሩ ግን ቀላል መልስ የለውም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

"በሁሉም መድሀኒት እና በሰው ሕይወት ውስጥ የተዘረጋ ሁለገብ ችግር ነው" ብለዋል።

"አንቲባዮቲኮች በአካባቢያችን፣ በምግባችን በሁሉም ቦታ ይገኛሉ። እናም አንድ ነጠላ መፍትሄ ማምጣት ቀላል አይደለም።"

መድሃኒት የሚቋቋዑ ኢንፌክሽንን ለማስወገድ የተሻለው መንገድ ኢንፌክሽኑን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ነው። ይህም ማለት ከፍተኛ የክትባት ፣ የውሃ ንፅህና እና ዐኸዓዓዒ ንፅህና ያስፈልጋል ብለዋል።

" አንቲባዮቲኮችን የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች በመኖራቸው ተጨማሪ አንቲባዮቲኮች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። ነገር ግን በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን እና ትክክለኛዎቹ መድሃኒቶች መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን።"

በኪንግስ ኮሌጅ ለንደን የማይክሮ ባዮሎጂ ከፍተኛ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሊንዚ ኤድዋርድስ ይህ አዲሱ ጥናት "ከቀደመው መረጃ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እና አሳሳቢ እድገት ያሳየ ነው" ብለዋል።

"እነዚህ ግኝቶች ለዓለም አቀፍ የጤና መሪዎች እንደ ማንቂያ ደወል ሆነው ሊያገለግሉ ይገባል። ወሳኝ እርምጃ ካልተወሰደ ኤኤምአር በሕጻናት ጤና ላይ በተለይም በዓለም ላይ በጣም ተጋላጭ በሆኑ ቀጠናዎች ውስጥ በአስርት ዓመታት የተመዘገበውን እድገትን ሊቀለብስ ይችላል ። "