"አባቴ እስር ቤት መሞት አለበት" እናቷን ከ50 በላይ ወንዶች ያስደፈረው ግለሰብ ልጅ

ወቅቱ ኅዳር፣ 2013 አመሻሽ ላይ ነበር ሕይወቷን ላይመለስ ያጨለመው ስልክ የተደወለላት።
እናቷ ጂዜል ፔሊኮት ነበረች የደወለችላት።
"በዚያች ዕለት እናቴ፣ ዶሚኒክ [አባቴ] ለአስር ዓመታት ያህል እያደነዘዘ በተለያዩ ወንዶች ያስደፍራት እንደነበር መረዳቷን ነገረችኝ" ትላለት ካሮላይን ዳሪያን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ።
ካሮላይንን ይህንን ስትሰማ "የሕይወትን ትርጉም አጣሁ" ትላለች።
"ጮህኩኝ፣ አለቀስኩኝ፣ ሰድቤውም እንደነበር አስታውሳለሁ" የምትለው ካሮላይን ሁኔታውን የመሬት መንቀጥቀጥ ያህል እና እንደ አስፈሪ አውሎ ንፋስ ነው የምትገልጸው።
ባለቤቱን ለዓመታት እያደነዘዘ የደፈረው እና ከ50 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ያስደፈረው ዶሚኒክ ፔሊኮት ታሪካዊ በተባለ እና ለሦስት ወር በዘለቀው የፍርድ ሂደት ጥፋተኛ ተብሎ የ20 ዓመት እስር የተፈረደበት በታኅሣሥ ወር ነበር። ካሮላይን አባቷ "በእስር ቤት መሞት አለበት" ትላለች።
ዶሚኒክ የደነዘዘች ሚስቱን መጥተው እንዲደፍሩ በበይነ መረብ የመለመላቸው ሃምሳ ወንዶች ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ናቸው ሲል የእስር ቅጣት አስተላልፎባቸዋል።
ሁኔታው ይፋ የሆነው ግለሰቡ በአንድ መደብር ውስጥ ተደብቆ የሴቶች ቀሚስ ስር ፎቶ ሲያነሳ በመያዙ ነበር።
በዚህም ነበር የግለሰቡ ኮምፒውተር የተፈተሸው።
ጄዚል ፔሊኮትን የቀድሞ ባለቤቷ እያደነዘዘ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች ለዓመታት አስደፍሯታል።
ይህም ለአስር ዓመታት ያህል የተፈጸመ ሲሆን፣ ግለሰቡ ባለቤቱን በተደጋጋሚ የደፈረበትን እና የማያውቋትን ወንዶች እያጋበዘ ያስደፈረባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ኮምፒውተሩ ላይ ተገኝተዋል።
ለአምስት አስርት ዓመታት በትዳር አብራው የኖረችው ባለቤቷ ከ80 በላይ በሚሆኑ ወንዶች እንዳስደፈራት እና ድርጊቱን እንደቀረጸው የተረዳችው ከፖሊስ ነው።
በመድፈር ወንጀሉ ላይ የተሳተፉት ወንዶች ቁጥር ብዛት ፈረንሳይን አስደንግጧል።
በቪዲዮው ላይ ከታዩት 83 ወንዶች መካከል ፖሊስ መለየት የቻለው 50ዎቹን ብቻ ነው።
ዕድሜያቸው ከ26 እስከ 68 ሲሆን፣ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ያሉ ናቸው። የእሳት አደጋ ሠራተኞች፣ ፋርማሲስቶች፣ ነርስ፣ የእስር ቤት ጠባቂ፣ ጋዜጠኞች ተካተውበታል። በርካቶች የልጆች አባት እና ባለትዳሮች ናቸው።
አንደኛው ኤችአይቪ በደሙ መኖሩን እያወቀ ስድስት ጊዜ እንደደፈራት ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ምንም እንኳን በሽታው ባይተላለፍባትም ሌሎች በወሲብ በሚተላለፉ በሽታዎች ተይዛ እንደነበር የጤና ባለሙያ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የጤና እክሎች እንደተከሰቱባት ተገልጿል።
የዶሚኒክን ዘግናኝ ወንጀሎች በታየው በዚህ ችሎት የመድፈር እና ፆታዊ ጥቃቶችን ጎልቶ እንዲታይ ከማድረግ በተጨማሪ ብዙም ስለማይታወቅ በመድኃኒት በማደንዘዝ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ውይይት እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ካሮላይን በአሁኑ ወቅት በአደንዛዥ ንጥረ ነገሮች የሚደገፍ ጥቃትን መታገል የሕይወቷ ጥሪ አድርጋዋለች። አደንዛዥ ንጥረ ነገር እንዲወስዱ ተደርገው የሚደፈሩ ተጎጂዎች ጥቃታቸውን ስለማያስታውሱ እና መደንዘዛቸውንም ላያውቁ ስለሚችሉ ብዙ ጊዜ ሪፖርት አያደርጉም።
ዳሪያን የተጎጂ ሴቶች ድምጽ እንዲሰማ እየታገለች ትገኛለች።
የእናቷን ልብ የሚሰብር የስልክ ጥሪ ተከትሎ ባሉት ቀናት ካሮላይን እና ወንድሞቿ ፍሎሪያን እና ዴቪድ ከእናታቸው አጠገብ ለመቆም ወደ ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ደቡባዊቷ ፈረንሳይ፣ ማዛን አቀኑ።
አሁን ካሮላይን እንደምትለው "ባለቤቷ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ ከታዩ የከፉ ደፋሪዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን" እናቷ የተረዳችበት አሳዛኝ ወቅት መሆኑን ትናገራለች።
ብዙም ሳይቆይ ራሷ ካሮላይን በፖሊስ ተጠርታ ሌላ ዓለሟን የሚያጨልም ክስተት ሰማች።
ፖሊሶች ከአባቷ ላፕቶፕ ተገኙ ያሏትን ሁለት ፎቶዎች አሳይዋት። በዚህም ምሥል ላይ አንዲት ቲሸርት እና ሙታንታ ብቻ የታጠቀች ራሷን የሳተች ሴት አልጋ ላይ ተንጋላ ትታያለች።
መጀመሪያ ላይ ይህች ግለሰብ ራሷ እንደሆነች ማወቅ አልቻለችም ነበር።
"ራሴን ማወቅ እንኳን ተሳነኝ" ትላለች ካሮላይን።
ከዚያም የፖሊስ መኮንኑ "በጉንጭሽ ላይ ያለው ተመሳሳይ ቡናማ ምልክት በፎቶው ላይ አለ፤ አንቺ ነሽ። ከዚያም ሁለቱን ፎቶዎች በተለየ መንገድ ተመለከትኳቸው። እንደ እናቴ በሁሉም ፎቶዎቿ ላይ እንደምትታየው በግራ ጎኔ ተኝቼ ነበር" ትላለች።
ካሮላይን አባቷ እንደደፈራት እርግጠኛ መሆኗን ትናገራለች። አባትየው ይህንን ጉዳይ ቢክድም የልጁን የተጋለጡ ፎቶዎችን በተመለከተ የሰጣቸው ማብራሪያዎች እርስ በርስ የሚጣረሱ ናቸው።
"እንዳደነዘዘኝ አውቃለሁ፣ ምናልባትም ለፆታዊ ጥቃት ነው። ነገር ግን ምንም ዓይነት ማስረጃ የለኝም" ትላለች።
አባትየው ባለቤቱን ያደረጋትን የሚያሳዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ቢኖሩም በልጁ ላይ ግን ምንም ማረጋገጫ አልተገኘም።
አባትየው ሚስቱን ከደፈሩት ተከሳሾች መካከል ዣን ፒየር ማርቻል የተባለውን ግለሰብ ባለቤት በመድፈር እንዲሁም የሴት ልጁን ካሮሊን እና የልጆቹን ባለቤቶች የተጋለጡ ምሥሎች በማንሳት ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
"ለበርካታ የጉዳት ሰለባዎች ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አይታመኑም። ምክንያቱም ምንም ማስረጃ የለም። የሚሰማቸው የለም እንዲሁም ድጋፍ አያገኙም" ስትል ትገልጻለች።
አባትየው በእናቷ ላይ የፈጸማቸው የሚዘገንኑ ወንጀሎች ይፋ ከሆኑ በኋላ ካሮላይን ይህንን በሚመለከት መጽሐፍ ጽፋለች።
"I'll Never Call Him Dad Again" (መቼም ቢሆን አባዬ ብዬ አልጠራውም) በሚል የደረሰችው ይህ መጽሐፍ በአባትየው አጸያፊ ተግባር ምክንያት የደረሰውን የቤተሰቧን ሰቆቃ የሚተርክ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአደንዛዥ ንጥረ ነገሮች ድጋፍ የሚደረግን ጥቃት በጥልቀት ይዳስሳል።
"የህመም ማስታገሻዎች፣ ማደንዛዣዎች ሁሉም መድኃኒቶች ናቸው" የምትለው ካሮላይን በተለይም በማደንዛዣ ድጋፍ የሚደረጉ ጥቃቶች በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ናቸው ትላለች።
እናቷ ከ200 ጊዜ በላይ ከመደፈሯ ባለፈ ግለሰቡ በልጇ ላይ ጥቃት አድርሶ ሊሆን እንደሚችል ለመቀበል እንዳስቸገራት ትናገራለች።
"ለእናቴ ይህንን ሁሉ መከራ በአንድ ጊዜ መቀበል ከባድ ነው" ትላለች።
ጥቃቱ የተፈጸመባት የ72 ዓመቷ ጂዜል ፔሊኮት የፈረንሳይ ሕግ የሰጣትን ማንነቷን የመደበቅ መብቷን በመተው ታሪኳንም ሆነ ራሷን ለሕዝብ ይፋ አድርጋለች።
ጂዜል ታሪኳን እንዲሁም ማንነቷን በማውጣት ድፍረቷን እንዲሁም ጀግንነቷን አሳይታለች።
"በጣም አሰቃቂ እና ዘግናኝ ቢሆንም በክብር እና በጥንካሬ ማለፍ ነበረብን" ስትል ታስረዳለች።
በአሁኑ ወቅት ካሮላይን ዘግናኝ ድርጊቶችን የፈጸመው የደፋሪው ግለሰብ እና በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃቶች የተፈጸመባት እናት ልጅ መሆኗን አስታርቃ እንዴት መኖር እንዳለባት መረዳትን "አስፈሪ ሸክም" ስትል ትገልጸዋልች።
በአሁኑ ወቅት አባዬ የማትለው እና ዶሚኒክ እያለች የምትጠራው ግለሰብ በልጅነቷ የነበረውን ሚና በጭራሽ ማሰብ አትፈልግም።
"ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው፣ አስበው የነበረውን አባቴን አላየውም። ማየት የምችለው ይህንን ወንጀለኛ እና ደፋሪ ግለሰብ ነው" ስትል ታስረዳለች።
ካሮላይን ሌሎች "ጭራቅ" ብለው የሚገልጹበትን አገላለጽ ብዙ እንደማትቀበለው ትናገራለች።
በተቃራኒው "ያደረገውን ነገር ጠንቅቆ የሚያውቅ እና በጭራሽ ያልታመመ" ትላለች።
"እሱ አደገኛ ሰው ነው። በጭራሽ ከእስር የሚወጣበት መንገድ መኖር የለበትም፤ በጭራሽ" በማለት የአባቷ ፍጻሜ በእስር ቤት እንዲሆን እንደምትሻ ትናገራለች።
ሃያ ዓመት በእስር እንዲማቅቅ የተፈረደበት የ72 ዓመቱ ዶሚኒክ ፔሊኮት ዳግም ቤተሰቦቹን ላያይ ይችላል። እናት እና ልጆቿ ከዚህ ሰቆቃ እና መከራ ለማገገም እየሞከሩ ይገኛሉ። እሷም ባለቤቷ፣ ወንድሞቿ እና የ10 ዓመት ወንድ ልጇ "ብርታትን ይሰጡኛል" ትላለች።