የካንሰር ሕሙማንን ለማከም የሚውለው መድኃኒት አዎንታዊ ውጤት ማሳያቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, SPL
ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረ የጭንቅላት እና የአንገት ካንሰር ያለባቸው ሰዎች ችግሩ በድጋሚ ሳይከሰት ለረጅም ጊዜ እንዲኖሩ የሚያስችል መድኃኒት ላይ የተደረገው ሙከራ አዎንታዊ ውጤት ማሳየቱን ተመራማሪዎች ገለጹ።
በመድኃኒቱ ጥናት ላይ የተሰማሩ ሳይንቲስቶች እንዳሉት ለማከም አስቸጋሪ ከሆነው ካንሰር ጋር ለ20 ዓመታት ለኖሩ ሰዎች የመጀመሪያ ተስፋ የፈነጠቀ ነው ብለዋል።
ከስድስት ዓመታት በፊት ከበሽታው የመትረፍ ዕድሏ ጠባብ እንደሆነ እና እየተስፋፋ የሚሄድ የምላስ ካንሰር እንዳለባት የተነገራት የ45 ዓመቷ ላውራ ማርስተን በዚህ ዜና ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች።
በጭንቅላት እና በአንገት አካባቢ የሚከሰተውን ካንሰር ማከም በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሽታውን ለማከም በሚደረገው ሂደት ውስጥ ይህ ነው የሚባል የጎላ ለውጥ ሳይታይ ቆይቷል።
በጭንቅላት እና በአንገት ላይ በሚከሰተው እየተስፋፋ በሚሄደው ካንሰር ከተያዙት ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት በአምስት ዓመታት ውስጥ ለህልፈት ተዳርገዋል።
ካንሰርን ለማከም አዲስ መንገድን ለመፈለግ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጥረት አካል የሆነው እና በለንደን የካንሰር ኢኒስቲቲዩት እየተካሄደ ባለው ሥራ ተሳታፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ኬቪን ሃሪንግተን በመድኃኒቱ ላይ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Laura Marston
በዚህ ሂደት ካንሰር ያለበት ክፍል ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል ብቃቱን በማዳበር የካንሰር ህዋሳትን እንዲዋጋ የሚያስችል አቅም እንዲፈጠር በማድረግ ዕባጩ የሚወገድ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ መድኃኒቱ በሽታን የመከላከል አቅምን ለማጠናከር እስከ አንድ ዓመት ድረስ ይሰጣል።
አዲሱ ዘዴ አዎንታዊ ውጤትን አሳይቷል። መድኃኒቱ የሚሰጣቸው ሕሙማን ከሦስት ዓመታት በኋላ ካንሰሩ በሌላው የአካላቸው ክፍል ላይ የመከሰት ዕድሉ በ10 በመቶ ይቀንሳል።
በመድኃኒቱ ሙከራ ላይ የተሳተፈችው ላውራ በመድኃኒቱ ምክንያት በሕይወቷ ተስፋ እንደተፈጠራላት እና እስካሁንም ለመቆየቷ ምክንያት መሆኑን ተናግራለች።
ይህ ሕክምናም "በአስደናቂ ሁኔታ ሕይወቴን መልሶልኛል" ስትል የተመለከተችውን ለውጥ ገልጻለች።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በሕክምናው ሂደት ለተገኘው ውጤት ቁልፉ ነገር ካንሰሩ በተከሰተበት ቦታ ላይ ቀዶ ሕክምና ከመደረጉ በፊት መድኃኒቱ መሰጠቱ ነው።
ይህም ካንሰሩ ተመልሶ እንዳይመጣ ለማድረግ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም እንዴት መዋጋት እንዳለበት እንዲለማመድ ያደርጋል።
ይህ የሕክምና ዓይነት በካንሰር የተያዙ ሕሙማንን "ዓለም በበጎ ሁኔታ ሊቀይረው ይችላል" ሲሉ ፕሮፌሰር ሃሪንግተን ተናግረዋል።
"በሽታው በሰውነት ውስጥ እንዳይስፋፋ [መድኃኒቱ] በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰዋል። በሂደትም ከማይታወቅበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ያስችላል" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
በየዓመቱ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 12,800 የሚሆኑ አዳዲስ የጭንቅላት እና የአንገት የካንሰር ምርመራ ውጤቶች ይመዘገባሉ።
ይህ ሕክምና በተለይ በአንዳንድ ሕሙማን ላይ በጥሩ ሁኔታ ውጤታማ ሲሆን፣ በሙከራው ላይ በተሳተፉ በሁሉም ታማሚዎች ላይ መሥራቱ ደግሞ "በጣም አስደሳች ነው" ያሉት ፕሮፌሰር ሃሪንግተን አሁን መድኃኒቱ ለሕክምና መቅረብ እንደሚችል አመልክተዋል።
የዚህ ጥናት ግኝቶች በዓመታዊው የአሜሪካ የካንሰር ሕክምና ማኅበር ስብሰባ ላይ ቀርቧል።