የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር አገራቸው በጭራሽ ለሽያጭ እንደማትቀርብ ለዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ማክሰኞ ዕለት በዋሺንግተን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ፣ ካናዳን 51ኛ የአሜሪካ ግዛት ለማድረግ እንደሚፈልጉ ለተናገሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገሬ "ለሽያጭ አትቀርብም" ሲሉ ተናገሩ።
ባለፈው ሳምንት ምርጫ ያሸነፉት ማርክ ካርኔይ በካናዳ ምርቶች ላይ ታሪፍ የጣሉትን እና ካናዳን የአሜሪካ የግዛት አካል የማድረግ እቅድ እንዳላቸው የተናገሩትን ዶናልድ ትራምፕን "ለመጋፈጥ" ቃል ገብተው ነበር።
የቀድሞው የባንክ ገዢ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላቀረቡት ካናዳን የዩናይትድ ስቴትስ አካል ማድረግ "ምርጥ ጋብቻ" ጥያቄ ኮስተር ያለ ግን የተመጠነ ምላሽ ሰጥተዋል።
ምንም እንኳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሁለቱ ጎረቤት አገራት ግንኙነት ንፋስ ቢገባውም ሁለቱ መሪዎች በኦቫል ኦፊስ ሲገናኙ እርስ በእርስ ተሞካሽተዋል።
ትራምፕ በካናዳ እና ሜክሲኮ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን የተወሰኑት ድርድር እስኪደረግ ድረስ በሚል እንዲዘገዩ ተደርገዋል።
ካናዳ ፌንታኒል የተሰኘውን አደንዛዥ ዕጽ ግዛቷን አልፎ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ ማድረግ አልቻለችም ሲሉ የሚወቅሱት ዶናልድ ትራምፕ በብረት እና አሉሚኒየም ምርቶቿ ላይ ታሪፍ ጥለዋል።
ካርኔይ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የተገናኙት ባለፈው ሳምንት የአገሪቱን ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ በጎ ቃላትን የተለዋወጡ ሲሆን ትራምፕ ካርኔይን "በጣም ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው" ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ካርኔይ በምርጫ ማሸነፋቸውንም በማስመልከት "በፖለቲካ ዳግም የመመረጥ ታሪክ ትልቁ ነው፤ ምናልባት ከኔም ሳይበልጥ አይቀርም" ብለዋል።
ካርኔይ በበኩላቸው ትራምፕን "የለውጥ ፕሬዝዳንት" ካሉ በኋላ "ያለ ማቋረጥ የአሜሪካዊ ሠራተኞች ላይ ትኩረቱን ያደረገ፣ የድንበሮቿን ደኅንነት ያስጠበቀ፣ እና ቃሉን የሚጠብቅ" ካሉ በኋላ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳንን "ዳግም እንዲያንሰራራ ያደረጉ" ብለዋቸዋል።
በሁለቱ መካከል ያለው አለመግባባት ዳግም የጀመረው ዶናልድ ትራምፕ ካናዳ በአሜሪካ ስር ብትሆን የተሻለ እንደሚሆን ከተናገሩ በኋላ ነው።
ካርኔይ በሚገባ የተጠና ምላሽ ይዘው የመጡ መሆናቸውን ያሳዩት ከሪል ስቴት እንደሚያውቁት "ለሽያጭ የማይቀርቡ የተወሰኑ አካባቢዎች አሉ" ሲሉ ለዶናልድ ትራምፕ ምላሽ ሲሰጡ ነው።
"ባለፉት ወራት ባካሄድኩት የምርጫ ዘመቻ ወቅት የካናዳን ባለቤቶች እንደማግኘቴ ለሽያጭ አትቀርብም፤ ለሽያጭ የምትቀርብ አይደለችም፤ በጭራሽ!" ብለዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው "በጭራሽ ብሎ መደምደም ጥሩ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በኦቫል ኦፊስ ከካርኔይ ጋር በነበራቸው ንግግር ታሪፍ ለማንሳት የሚያስችል ውይይት አድርገው እንደሆን በጋዜጠኞች ሲጠየቁ "ምንም የለም። ሁሉም ባለበት ነው" ሲሉ መልሰዋል።
አክለውም "ወዳጅነት የተሞላበት ንግግር ነበር ያደረግነው" ካሉ በኋላ "ነገር ግን የራሳችንን ተሽከርካሪዎች ለማምረት ነው የፈለግነው" ብለዋል።
ትራምፕ አሜሪካ የካናዳን ወታደራዊ ኃይል እንደምትደጉም ዳግም ተናግረው ከካናዳ የሚመጡ አሉሚኒየም እና ብረት ግን እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።
ከካርኔይ ጋር ባደረጉት ውይይት "ጠንካራ ነጥቦች" ማንሳታቸውን የገለፁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ነገር ግን "በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከካናዳ ጋር ወዳጅ ሆነን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ካርኔይ በበኩላቸው ዶናልድ ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ እንዲያነሱ "አጥብቀው መወትወታቸውን" ተናግረው ለመደራደር ፈቃደኛ ሆነው እንዳገኟቸው ገልጸዋል።
ካርኔይ በግልጽ ቀኑን ባያስቀምጡም ሁለቱ መሪዎች በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ዳግም ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ካርኔይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካናዳ የዩኤስ ግዛት እንድትሆን የሚያደርጉትን ጥሪ እንዲያቆሙ መጠየቃቸውን ተናግረው "ምኞትን ከእውነታው" መለየት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
"ፕሬዝዳንት ናቸው። የራሳቸው ሰው ናቸው" ያሉት ካርኔይ "በሁለት ሉዓላዊ አገራት መካከል ድርድር እየተካሄደ እንደሆነ ይረዳሉ" ብለዋል።