ታዋቂዋ ቲክቶከር 'ላይቭ' ላይ እያለች በጥይት ተገደለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የ23 ዓመቷ ሚክሲኳዊት የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ የቲክቶክ ቀጥታ ሥርጭት ላይ እያለች በተተኮሰባት ጥይት መገደሏን የምትኖርበት ግዛት ኸሊስኮ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
እንደ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤቱ ገለጻ ቫሌሪያ ማርኬዝ የተገደለችው አንድ ሰው ጓደለሃራ ከተማ ወደሚገኘው የተጽእኖ ፈጣሪዋ የውበት ሳሎን በመግባት "ሽጉጥ ከተኮሰባት" በኋላ ነው።
ግድያው የተፈጸመበት ምክንያት እስካሁን ባይደረስበትም ጉዳዩ የሴት ልጅ ግድያ (femicide) ምድብ ውስጥ ተካትቶ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
ይህ የግድያ ምድብ ሴቶች እና ልጃገረዶች በፆታቸው ምክንያት የሚፈጸምባቸው ግድያ የሚመረመርበት የወንጀል ዘርፍ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት በየቀኑ 10 ሴቶች በአጋራቸው ወይም የቤተሰብ አባላቸው እንደሚገደሉ በሚገልጽባት ሜክሲኮ፤ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እጅጉን የተለመደ ነው።
ሟች ማርኬዝ ግድያው ከመፈጸሙ ደቂቃዎችን አስቀድሞ ዛፖፓን በተባለው ከተማ በሚገኘው የውበት ሳሏኗ ውስጥ አሻንጉሊት ይዛ ጠረጴዛ ላይ ቁጭ ብላ በቲክቶክ ላይ የቀጥታ ሥርጭት እያስተላለፈች ነበር።
ቲክቶከሯ ጥቃቱ ከተፈጸመባት በቅጽበት ውስጥ በጥይት የተገደለች ሲሆን፣ ቪድዮው ያበቃው አንድ ሰው ስልኳን አንስቶ ቀረጻውን ሲያቆመው ነው።
የሜክሲኮ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ወጣቷ የተገደለችው ስጦታ ይዞላት እንደመጣ ባስመሰለ ሰው በተፈጸመባት ጥቃት ነው።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በቦታው የደረሰው ፖሊስ ማርኬዝ ሕይወቷ ማለፉን ማረጋገጡን የግዛቲቱ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ እስካሁን በወጣቷ ላይ ግድያውን ፈጽሟል ተብሎ የተጠርጣሪውን ግለሰብ ስም አልገለጸም።
ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ በድምሩ 200 ሺህ ገደማ ተከታዮች ያሏት የማርኬዝ አድናቂዎች፤ በአሰቃቂው አሟሟቷ ተደናግጠዋል።
የዛፖፓን ከተማ ከንቲባ ሁዋን ሆዜ ፍሬንጂ፤ ማርኬዝ ለዚህ ሊያደርሳት የሚችል ስጋትን በተመለከተ ከባለሥልጣናት እርዳታ እንዲደረግላት የተጠየቀ ምንም ሪፖርት እንዳልነበረ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ከንቲባው ግድያውን በማስመለክት "የሴት ልጅ ግድያ በጣም አስከፊ ነገር ነው" በማለት ድርጊቱን ኮንነውታል።
የፎረንሲን ባለሙያዎች ግድያውን እየመረመሩ መሆኑን የግዛቲቱ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።