'የራሳቸውን ሕዝብ በፍርሃት የሸበቡ . . . ስለኢትዮጵያ ማውራት ባህሪያቸው ነው' - የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force/fb

የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ

"ሀገር ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ" ሀገራት "በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር መሞከራቸው የተለመደ ባህሪ እንደሆነ እናውቃለን" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ ተናገሩ።

የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በስም ያልጠቀሷቸው አካላትን "ምክር እየሰሙ ብድግ ብድግ ለሚሉ ትናንሽ ኃይሎች የተደራጀ" እንዳልሆነም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ ይህንን የተናገሩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሀገሪቱ የነጻነት በዓል ላይ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው ኢትዮጵያን የተመለከተ ንግግር ካሰሙ ከሳምንት በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 16/2017 ዓ.ም. በተከበረው 34ኛው የኤርትራ ነጻነት በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጠንካራ ትችት ሰንዝረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ፤ "የውጭ ኃይሎች በብልፅግና ወኪላቸው አማካኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት ያወጁት ጦርነት ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ የሚያሳይ ነው" በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት "የጦር መሳሪያ ግዢ እና የወታደራዊ ዝግጅት" ላይ ነው ሲሉ የከሰሱት ኢሳያስ፤ "እነዚህ የታቀዱ ጦርነቶችን ለማስጀመር የጦር መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጅዎችን ለማግኘት የሚደረገው የግዢ ጥድፊያ፣ ተጓዳኝ ፉከራዎች እና ወታደራዊ ዝግጅት ሁሉም ያወቀው እና የመዘገበው ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

"ሊያቀርቡ የሚፈልጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ" ነው በማለት ከስሰዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተለይም "የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ" በማለት የሰነዘሩት ሃሳብ ከተለያዩ አካላት ጠንካራ ምላሾችን አስከትሏል።

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ ቅዳሜ ግንቦት 23/2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቀረበ ቃለ መጠይቅ ላይ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ምላሽ የሚመስል ትችት አንስተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ በስም ያልጠቀሷቸውን አካላት ኢትዮጵያን የተመለከተ ንግግር ማድረጋቸውን በማመልከት ወቅሰዋል።

ሚኒስትሯ ንግግር አድርገዋል ያሏቸውን አካላት የገለጹት፤ "በራሱ ሀገር ነው ብለህ ለመጥራት የሚያስቸግር፣ የራሱን ሀገር ሕዝብ በፍርሃት ተሸብቦ የሚኖርበት፣ በተቻለ አጋጣሚ ሀገር ለቆ የሚወጣባቸው ሀገራት" በማለት ነው።

"በዚህ ልክ ስለ ኢትዮጵያ ለመናገር [ሙከራ] ማድረጋቸው የተለመደ የእነርሱ ባህሪ እንደሆነ እናውቃለን" ብለዋል።

"በአሁኑ ሰዓት እየተገነባ ያለው ሠራዊት እነርሱ እንደሚያስቡት እዚህ ሰፈር ላይ . . . የእነሱን ምክር እየሰሙ ብድግ፣ ብድግ ለሚሉ ትናንሽ ኃይሎች የተደራጀ ሠራዊት አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ፤ "በማንኛውም የተሳሳተ ስሌት ኢትዮጵያን ለመድፈር፣ ብሔራዊ ጥቅሟን ለመንካት ለሚፈልጉ ኃይሎች በአስተማማኝ ሁኔታ የተገነባ" እንደሆነም ገልጸዋል።

"ቤታችን ውስጥ ላሉት እዚያም እዚህም ለሚታዩት ትንንሽ ነገሮች የሰፈር ሚሊሻ በቂ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህንን የሚሊሻ ኃይልም "እያሰለጠኑ" እና "እያዘጋጁ" መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ

የፎቶው ባለመብት, ENA/YouTube

የምስሉ መግለጫ, የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ባለፉት ዓመታት በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ተደርገዋል ያሏቸውን የሪፎርም ሥራዎች ያነሱት አይሻ፤ "ያለው ነባራዊ ሁኔታ፣ ዓለም አቀፍ ሴናሪዮው [ሁኔታው] ራሱ የሚፈልጋቸው ዝግጁነቶች ስላሉ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አደረጃጀቶች" መፈጠራቸውን አመልክተዋል።

ከእነዚህ አደረጃጀቶች መካከልም "ባሕር ኃይል፣ ልዩ ዘመቻ፣ የሳይበር ሴኪዩሪቲ" እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ያሉትን ግጭቶች በተመለከተም በቃለ መጠይቁ ተናግረዋል።

ክልሎቹ ከዚህ ቀደም የነበሩበት ሁኔታ "ሁሉም ሰው የሚረዳው" እንደነበረ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ "አካባቢዎቹ በተነጻጻሪ ሰላም እና መረጋጋት የሚታይባቸው፣ ሕዝብ ተረጋግቶ ወደ ልማት ሥራ የገባባቸው ሁኔታዎች ናቸው ያሉት" ብለዋል።

የፋኖ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቁመና "እዚህ ግባ" የሚባል እንዳልሆነ እና "ለመከላከያ ሠራዊት ስጋት የሆነ" ወይም "ሕዝቡ ከሰላማዊ ኑሮው መቶ በመቶ ተነጥሎ እንደነበረው የሚያደርግ" እንዳልሆነ በቃለ መጠይቁ ተናግረዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ "ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል" ለማድረግ የየክልሎቹን ሚሊሻ እና የፀጥታ ኃይል የማሠልጠን ሥራ እየተከናወነ መሆነን አንስተዋል። "[ከክልሎቹ] አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ የማገዝ ሥራ እየሠራ፤ አካባቢዎቹን ወደ ማረጋጋት እና ራሱ [ሠራዊቱ] ወደነበረበት የሀገር ህልውና ጠባቂ ቁመና የመመለስ ሥራ ጎን ለጎን እየተሠራ ነው" ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በንጹሃን ዜጎች ላይ ወስዷቸዋል ስለተባሉ እርምጃዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስትሯ፤ ጉዳዩ "የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ" እንደሆነ በመግለጽ ክሱን አጣጥለዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ "እንደሚባለው ሄዶ የሚጨፈጭፍ ኃይል ቢሆን ኖሮ እነዚያም እስካሁን እየተሽሎከለኩ ይቆዩ ነበር የሚል ዕምነት የለኝም" ያሉት አይሻ፤ ይህ ማለት ግን "የሚፈጠረ ነገር አይኖርም ማለት አይቻልም" ብለዋል።

ሚኒስትሯ፤ "በሚደረጉ የሰላም ማስከበር ሂደቶች ውስጥ ሰው አይሳሳትም ማለት አይቻልም፤ የሚኖረውን ነገር ስለምናውቀው" በማለት ተናግረዋል።

በተቃራኒው ወገን ያለው ኃይልም "በሕዝብ ውስጥ ተሰግስጎ፣ ሕዝበን መስሎ፣ ከሕዝብ ነጥለህ [እርምጃ ለመውሰድ] የሚያስቸግር ዓይነት ስልት የሚከተል ስለሆነ የሚደርሱ አንዳንድ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ" ሲሉ ተደምጠዋል።

ሚኒስትሯ አይሻ ይህንን ቢሉም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በጦርነት አውዶች ውስጥ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች 'ንጹሃን ላይ ፈጽመዋል' ያሏቸውን ግድያዎች የተመለከተ በተደጋጋሚ ሪፖርቶችን ማውጣታቸው አይዘነጋም።

ኢሰመኮ በጥር ወር ባወጣው ሪፖርት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች አሳሳቢነታቸው እንደቀጠለ አስታውቆ ነበር።

ሪፖርቱ በአማራ ክልል በንጹሃን ላይ ግድያ እንደተፈጸመባቸው ከጠቀሳቸው አካባቢዎች መካከል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ እና ደባይ ጥላት ወረዳዎች እንዲሁም ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ይገኙበታል።