ስኮትላንድ ውስጥ በአሜን ተክላይ ግድያ የተጠረጠሩ ሁለት ታዳጊዎች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Police Scotland
በስኮትላንድ ግላስጎው አሜን ተክላይ ከተባለ ታዳጊ ግድያ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ባደረገው ምርመራ የ14 እና የ15 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።
የ15 ዓመቱ አሜን ረቡዕ ዕለት በከተማው በሚገኘው ሴይንት ጆርጅ ክሮስ አካባቢ በክላሬንደን ጎዳና ላይ በተፈፀመበት ጥቃት በጽኑ ቆስሎ ተገኝቷል።
ምንም እንኳ የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች በስፍራው ቢደርሱም ሕይወቱ እዚያው ማለፉ ተገልጿል።
የስኮትላንድ ፖሊስ ሁለት ታዳጊዎችን ከግድያው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና ምርመራው መቀጠሉን አስታውቋል።
ፖሊስ ግድያው ከሌላ ነገር ጋር እንደማይያያዝ እና መርማሪዎች ለግድያው መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችን ለማጣራት "ሁሉንም አቅጣጫ እየመረመሩ" መሆናቸውን ተናግሯል።
አሜን ከአባቱ ጋር በግላስጎው ይኖር የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደም 'የመቆየት መብት' ተሰጥቶት እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
የ17 ዓመቷ እህቱ ዴሊና ተክላይ "አሜን የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት የማግኘት እና የቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ ዶክተር ወይም መሐንዲስ የመሆን ምኞት ነበረው" ብላለች።
አሜን "ወንድሜ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጓደኛዬም ነበር" ስትል ለቢቢሲ ስኮትላንድ ኒውስ ተናግራለች።
አክላም "በጣም ተወዳጅ ልጅ፣ በጣም ደግ እና ብሩህ ነበር" ብላለች።
አሜን በጆርዳን ሂል በሚገኘው ሴይንት ቶማስ አኩዊናስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበር።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ክሌር ማኪንሊ ሞቱ "ለትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ አስደንጋጭ" ነበር ብለዋል።
የስኮትላንድ ፖሊስ በአሜን ግድያ ላይ ሰፊ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታውቋል።
ሱፐር ኢንቴንደንት ቼሪል ኬሊ እንዳሉት "መልሱ ያለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ነው" ካሉ በኋላ፤ ባልደረቦቻቸው የመንገድ ላይ ካሜራዎችን እየተመለከቱ እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ ጥያቄዎችን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም "በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ሀሳባችን ሁሉ ከአሜን ቤተሰቦች እና ወዳጆች ጋር ነው። ለእነሱ ልዩ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ፖሊስ ግድያውን በሚመለከት መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው ለዚህ ምርመራ ተብሎ በተከፈተው የመረጃ መቀበያ በኩል ጥቆማውን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።